In Memory

Social Media

 

እ ስ ቲ እ ና ስ ታ ው ሳ ቸ ው

የሩቅ፤ ቅርብ ሃዘን

የሩቅ፤ ቅርብ ሃዘን

በሉ እንዘክር አብረን፤

እናንት ሰማዕታት እንደምን አላችሁ ?

ከዓመታት በኋላ፤ ይኸው አሰብናችሁ

በአሜሪካ ምድር፤ ቀሪው ዘከራችሁ

ከእነ ልጆቻችን፤ ዛሬ አስታወስናችሁ።

ባልንጀሮቼ ፤ ቁሙ በተራ

አብሮ አደጎቼ፤ ቁሙ በተራ

ጎልማሳዎቹ ፡ ወጣት ልጆቼም ፤ ቁሙ በተራ

የሰማዕታቱን ስም፤ አንድ በአንድ እንጥራ።

ጌትነት የማነ፤ አንተ ፈር ቀዳጅ

የየካቲት ቤዛ፤ የቀበና ልጅ።

ከፍያለው ይሉሀል ቤተሰቦችህ

በእኛም በኩል ቢሆን ከፍ እንዳልክ ነህ።

የቀበና ውኃ፤ የዱቤ ባህር

አላየኸውም ወይ አክሊለ አባተን ?

የቀበና እናቶች ዘቅዝቁ ነጠላ

ለቆራጥ ልጃችሁ ለሙሉጌታ ሞላ።

ዴቭል ነው ይሉታል፤ እውነትም ዴቭል

ፍርሃት የማያውቅ ለሕዝብ ሲታገል

እንደወጣ ቀረ በዚያ መራር ትግል።

ብርሃነ ከበደን ማን ያውቃል በሠፈር

ዕይታን ሳይፈልግ የሞተ ለሃገር።

በለጠ፤ ኃብታሙ፤ የአቶ አየለ ልጆች

ለቀበና፤ ጎንደር የሆኑ ቤዛዎች።

ጎንደር ምን አወራ፤ በለሳ ጠለምት

ውርዬ መኮንን በክብር ሲሞት።

የሰው በላ ዘመን፤ ፍቅር ያልታደለ

እስቲ እንዴት ጨከኑ? በዘውዱ በቀለ።

አብዮት ዕብደት ነው ስሜት የሚያጋግል

ስለምን ይሞታል? ከበደ አጎናፍር ።

በአበሻ አገር፤ በምድረ አበሳ

ተሰቃይቶ አለፈ፤ ፀጋዬ ቶሎሳ።

አማኑዔል ጓዴ “አንቺ” የምልሽ

ሁሌ ይናፍቀኛል ደጉ ፈገግታሽ።

ታሪክ ጠይቅልኝ አፋኝ ስኳዱን

የት እንዳደረሰው ፍቃዱ ማሞን።

ሐምሌ ፲፩ ምሽት የጎዶሎ ቀን፤

እንጫወት ነበር የወጣት ወጉን፤

ከጎኔ ሲነጥቁኝ፤ ፍቄና አሥማረን።

 በሞቴ ጸጥ እንበል ፤ እስቲ አንዴ እናስታውስ

ከሁሉ ተግባቢ አሥማረ ሃጎስ

ፍቃዱ ማሞንም የኳስ መሃንዲስ ።

ሐምሌ ፲፩ ምሽት ጩኸት በረከተ፤ ተኩሱ በረከተ፤

በግርግሩ ውስጥ፤ ጋሽ ጥላሁን ሞተ።

ስንቱን ስሙን ልጥራ፤ ስንቱን ላስታውሰው፤

ሞገስ ማሞ በሉ የሸክላ ሜዳው።

ያንን ታጋይ ትውልድ ወቀሳ አታብዙበት

ፍትህ በማለቱ፤ ደም በገበረበት።

አይዞህ አንተ ትውልድ፤ ቀና በል ወገኔ

ከሕዝብ ጎን መቆም ፤ የለውም ኩነኔ ።

ጥሩንባ አልተነፋ፤ ቀብር አልተወጣ፤ ተዝካርም አላየን፤

በአጭሩ ሲቀሩ አብሮ አደጎቻችን፤

በቀረን አማራጭ፤ ከመንፈሳቸው ጋር ብዙ ዓመታት ኖርን።

ህይወት ጎዶሎ ነው፤ ለቀረነው ኁላ፤

ጓደኞች ላጣነው፤ በቀይ ሽብር ዱላ ።

እኒህ ከዚህ በላይ የዘረዘርኳቸው፤

በግፍ የተቀጩ፤ ሰማዕታት ናቸው፤

ከእኛ ከተለዩ፤ ከሰላሳ ዓመታት፤ በላይ የሆናቸው።

ከዚያም ወዲህ ቢሆን አጥተናል በርካታ

የቅርብ ኅዘናችን የእኛ ሮዛ ደስታ ።

ወርቁ ዳመና

ጁላይ 6 ቀን 2013 (እ ኤ አ)

ሜሪላንድ፤ አሜሪካ